ሀናዬ የጥንካሬ እና የፅናት ተምሳሌት

****❤️❤️❤️❤️****
ለሊት ነው በግምት 9 ሰአት …ትጸልያለች….ልጆቼን…ሁላችንንም በስማችን እየጠራች በሰመመን እሰማትና በሌላ ጎኔ እተኛለው። የወፎች ጫጫታ ስሰማ እነቃለው እስዋ አሁንም እዛው አልጋዬ ስር ትጸልያለች። ይገርመኛል ጽናትዋ አንድም ሳታቅዋርጥ ትጸልያለች……ቀና ብዬ ሳያት ጥቁር ፍሬም ያለውን መነጽርዋን አርጋ በተመስጦ አርጀት ያለውን መጽሃፍ ቅዱስዋን እያነበበች በ ቀይ እስክርቢቶ ታሰምራለች….እዛው እንደተኛው እያየዋት እስክትጨርስ እጠብቃታለው።

መጨረስዋን ሳውቅ ቁርስ ምን እንደምሰራ እጠይቃትለው። ፊትዋን ወደ ግድግዳ ዞር አርጋ አሰብ እያረገች ዘለግ ባለ ድምጽ ምን ይሻላል ትለኛለች እንደጨነቃት ይገባኝና የ ምርጫ አይነት እዘረዝራለው ዳቦ ይገዛ? ቂጣ ልጋግር? የማታ የተረፈ ግማሽ እንጀራ አለ እሱን ፍርፍር ላርገው? ሳቅ ትልና አንዱን ስሪ ትለኛልች….ትተማመንብኛለች….በኩራት ብድግ እልና ወደ ኩሽና ሄዳለው። እሰዋ እዛው ናት ታነባለች፤ትጽፋለች… አትሰለችም። ቁርስ ጨራርሼ በቁጥራችን ልክ ሰሃን ደርድሬ አከፋፍልና ሁሉንም ጠራቸዋለው ተስፋ፣ ፎቂ ፤በርዬ፤ዝሜ ይሰበሰባሉ …ግማሹ ሳሎን ያለው አልጋ ላይ ግማሹ በርጩማ ላይ የየግል ቁርሳቸውን ይዘው እስዋን ከ መኝታ ቤት ቀስ ብዬ እጠራታለው። ሞቅ ባለ ደማቅ ፈገግታ እየዘመረች በርዋን ከፍታ ትወጣለች። ለስዋ ቁሌት በዛ ካለበት ቀንሼ ያስቀመጥኩትን ሰጣታለው…ቀና ብላ እያየቺኝ ጌታእየሱስ ይባርክሽ የኔ ልጅ ደረሽልኝ እኮ….ትመርቀኛለች ውስጤን ታሞቀዋለች።

ቁርስዋን ጨርሳ እየዘመረች ጨርቆችዋን ታዘገጃጃለች….ዝማሬ ከአፍዋ አይጠፋም ትወዳለች….ምሳ ምን እንደምሰራ አልጠይቃትም ላስገርማት ከ ገዋሮ ጎመን ቆርጬ ጠባብሼ ቡና አፍልቼ ማቀራረብ ስጀምር እሰይ የኔ ልጅ እስቲ ሞቅ ሞቅ አርጊ ትለኛለች ደስተኛ ሳቂታ ሆና ስትውል ደስ ይለኛል። አቤት ማድነቅ ስትችልበት……ባለሞያ እኮ ነሽ ፓ! በጉርሻዋ ሁሉ ታደንቃለች ስትጨርስ ትመርቀኛለች ጌታየሱስ ይባርክሽ የኔ ሻንቆ …. ሻንቆዬ ትለኛለች እየሳቀች …ሻንቆ ስትለኝ አልወድም ግን ደስ ይለኛል።

አሁንም ያንን ጣቃ ጨርቅ ትቆራርጣለች በመቀስ ጫፉን ቆረጥ አርጋ ጥዝዝዝዝ በ እጅዋ ትቆራርጠዋለች አንዱን ስትጨርስ ፍቅርዬ ና አስቲ ያንን ጣቃ አምጣልኝ….ሁላችንንም አቆላምጣ ነው የምትጠራን። ቆራርጣ ስትጨርስ በኩራት ተቆራርጦ የተደረደረውን ጨርቅ እያየች ዛሬ ጎበዝኩ ከነጋ 9 ጋወን ቆራርጬ ጨረስኩ ትለኛለች። እንደ ግዋደኛ ስታወራኝ ደስ ይለኛል ትልቅነት ይሰማኛል።

አመሻሹን ጸሀይ ስትገባ ያቺን ጥቁረ አረንግዋዴ እና ነጭ መስመር መስመር ሻርፕ ደረብ አርጋ መጣው እስቲ እነ በሀብትዬ ጋ ደረስ ብዪ ብላኝ ትወጣለች። እስክትመለስ ለ እራት ተሰፋ እና ፎቂ ገዝተው የመጡትን ስካር ድንች ቀቅዬ ጠብቃታለው። ገና ከ በር ድምጽዋን ስንሰማ ሁላችንም ሳሎን የምንሰበሰበው ነገር አለ። በሃብትዬ ጋ እና ትጉ ጋ ደርሳ ስትመለስ እንጃ የሆነ ደስተኛ ሆና ነው የምትመጣው። ሳቅ ፈገግ እያለች ከ እነሱ ጋር የነበራትን ጊዜ ታወራናለች። ይገርመኛል ምንም ነገር ትነግረናለች ልክ እንደ ግዋደኞቾ…እስዋም ትላለች ዳሩ …ልጆቼ ግዋደኞቼ ናቸው…..ትላለች።

እራት ይቅረብ ወይስ ከ ፕሮግራም ቡሃላ መጅመሬያ ፕሮግራም እናረግ እነቅልፋቹ ይመጣል ትለናለች። መዝሙራችንን ዘምረን ከዛ እንደ ዲያሪ ከማየው መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ወደ ልብዋ የመጣውን ቃል ልጆቼ እያለች ታካፍለንና ስታጠቃልል…እና ልጆቼ ጌታ ሊመጣ ቅርብ ነው እንነጠቃለን ትለናለች። ይሄንን ቃል ስታካፍለን ልክ እንደ ታላቅ ፊልም ነበር የምስማት በታላቅ ናፍቆት ነበር የምታካፍለን። እንደተለመደው እጅ ለ እጅ ተያይዘን ስለ ቤታችን ስለ አባባ ስለ እምነቴ ስለ ዘመዶቻችን ስለ ሀገራችን ጸልየን እንጨርሳለን። የተቀቀለው ስክዋር ድንች በትኩሱ በትልቁ ትሪ ይቀርብና እያወራን እየተሳሳቅን እስክንጠግብ እንበላለን እስዋም በፍቅር እያየችን አብራን ትስቃለች። እራት አልቆ ሁላችንም ወደ እንቅልፍ እንሄዳለን እኩለ ሌሊት አልፎ ከ ሌሊቱ 9 ሰአት አከባቢ ትነቃለች…ትጸልያለች…አይደክማትም…..

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *