ምን አስተምራን አለፈች?

ሀናዬ የፍቅር ሰው ናት። እናቴ ብቻ ሳትሆን ጓደኛዬም ሚስጥረኛዬም ነበረች። ልጆቿ ሁሉ እንደጓደኛ ነው የሚቀርቧት። ከሰዎች ጋረ ተዋውቃ ለመግባባት እና ለመጫወት ደቂቃ አይፈጅባትም ነበር፤ በሄደችበት ሁሉ መልካም ጓደኞችን ታፈራለች። የልጆቿ ጓደኞች የሷም ጓደኞች ናቸው። በመልካምነቷ ሰውን ትገዛለች።

ጥንካሬዋ በጣም ከሚያስገርሙኝ ባህሪዋ አንዱ ነው።ያሰበችውን ለማሳካት ስህተት የሌለባቸውን መንገዶች ሁሉ ከመጠቀም ወደኋላ አትልም። አደርገዋለው ብላ ካሰበች ምንም አይዛትም! ታደርገዋለች! ሰዎች “ይህማ ይከብድሻል….” የሚሏትን ነገሮች እንኳን ከዳር አድርሳ ታስደንቃቸዋለች። ደካማነትን ሳይሆን ብርቱ መሆንን አውርሳናለች።

በአምላኳ ላይ ያላት መታመን ሌላው የሚያስደንቀኝ ማንነቷ ነው።ምንም አቅም ብታጣ፤ በእጇ አንዳች ባይኖር፤ “እግዚያብሄር ይችላል!” ነው መልሷ። ቢከፋት፣ ብታዝን፣ግራ ቢገባት በማንኛውም ጉዳዮች ላይ የመጀመርያ አማካሪዋ አምላኳ ነው። የጌታን መምጣት በጉጉት ከሚጠባነቁት ውስጥ አንዷ ናት። በቀን ውስጥ “ጌታ ይመጣል” ሳትል የዋለችበትን ቀን አላስታውስም። ከጓደኞቿ ጋርም ስታወራ የምሰማት ይህንኑ ነው። ሁሉም ልጆቿ (የወለደቻቸውም እናቴ ብለው የሚጠሯትም) የሆነ ነገር ሲያስቡ “ሀናዬ ጸልይልኝ” ይሏታል።የጸሎትን ታላቅ ሀይል አስተምራናለች።

ሃናዬ በጣም የምትደሰተው መንፈሳዊ ግጥም እና መዝሙር በመጻፍ፤ በመዘመር፤ መጽሀፍ ቅዱስ በማንበብ ነው። እሷን የሚያውቋት ሁሉ ይህንን ያውቃሉ። አንዳዴ ገና ከሆስፒታል እንደመጣው “ዛሬ የጻፍኩትን ግጥም ላንብብልሽ” ትለኛለች። እስካለፈችበት የመጨረሻ ቀን ድረስ ትጽፍ ነበር። ዛሬ ላይ ተመልሼ ጽሁፎቿን ሳነባቸው ልዩ ትርጉም ይሰጡኛል።

ሌላው በጣም የሚያስደንቀኝ ነገሯ ለልጆቿ ያላት የተለየ ፍቅር ነው። ለኛ ሳትሰስት ህይወትዋን ትሰጣለች። “የመኖሬ ምክንያት እናተ ናችሁ” ትል ነበር። የሆነ ግዜ “አሁን ሁላችሁም ቦታ ቦታ ይዛችኋል እኔ አሁን ምን እሰራለው?” ስትለኝ ደንግጬ ያንቺ መኖር የሚያስፈልገን ቦታ እስክንይዝ ብቻ አደለም እኮ ደሞ ለራስሽም መኖር አለብሽ ብዬ ተቆጣዋት፤ስቃ ዝም አለችኝ። እኛን ለማሳደግ በብዙ ችግር ውስጥ በማለፍ ትልቅ ዋጋ ከፍላለች። ለኔ የከፈለችው ዋጋ ደሞ ከሁሉም ይልቃል፤ማውራት ብጀምር ቀኑም አይበቃኝም፤ ባልጀምረው ነው ሚሻለው።

ሀናዬ ለስራ ብቻ ወደ ምድር የመጣች ሴት ትመስለኛለች። ግዜ ኖሯት ብዙ ተዝናንታ ባታቅም ነፋሻማ እና ተፈጥሮአዊ ቦታዎች ያስደስታታል። አሁን ባለኝ እረፍት አብረን የመዝናናት እቅድ ነበረን ግን በ ምድር ምን እረፍት አለ? የተሻለ ቦታ ሁሌም ከምትናፍቀው አምላኳ እቅፍ መሆኗን ሳስብ እጽናናለው። እኔም ግዜዬ ደርሶ ወደሷ እስከምሄድ ድረስ በየቀኑ እየናፈኳት እነቃለው። ያሳለፍናቸው ወርቃማ ትውስታዎች ለእድሜ ልክ እየመነዘርኩ የምደሰትባቸው ግዜዎች በመሆናቸው ፈጣሪን አመሰግነዋለው።

እናታችን፣ጓደኛችን፣ ሀናዬ እንወድሻለን!! እርስ በርሳችን በመዋደድ እና በመጠነካከር እንዳስተማርሽን እና እንዳሳየሽን እያደረግን በፍቅር እንኖራለን።